ግንቦት 23/2014 (ኢዜአ) የፌደራል የፍትህ እና የሕግ ኢንስቲትዩት ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ከ1 ሺህ በላይ መጻሕፍት አበረከተ።
ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት “ሚሊዮን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ” በሚል መሪ ሃሳብ ለአንድ ወር መጻሕፍት ለማሰባሰብ የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ተቋማትና ግለሰቦች በመለገስ ላይ ይገኛሉ።
በዛሬው እለትም የፌደራል የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲትዩት ከ1 ሺህ በላይ መጻሕፍት ለግሷል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ፤ መጽሃፈቱን በምርምር ዘርፍ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ምትኬ ሞላ አስረክበዋል፡፡
የተበረከቱት መጽሃፍት በተለይም ለጥናትና ምርምር አጋዥ የሆኑ የህግ መጻሕፍት መሆናቸው ታውቋል።
በዩኒቨርሲቲው የምርምር ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ምትኬ ሞላ፤ ምክንያታዊና መረጃ ያለው ትውልድ ለመገንባት የንባብ አማራጮችን ማስፋት ይገባል ብለዋል።
የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲትዩት ለአብርሆት ቤተ መጽሃፍት ላደረገውን ድጋፍ በማመስገን ትውልድ ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን አንዲወጣ ጠይቀዋል።
የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ከታህሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን የመጻሕፍት ማሰባሰብ ሥራውም ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ቤተ-መጽሐፍቱ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን መጻሕፍትን የመያዝ አቅም ያለው መሆኑ ይታወቃል።