Skip to content Skip to sidebar Skip to footer

ግንቦት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ያሰባሰበውን የተለያዩ ይዘት ያላቸው ከ5 ሺህ በላይ መጻህፍትን ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት አበረከተ።

“ሚሊዮን መጽሀፍ ለሚሊኒየሙ ትውልድ” በሚል መሪ ሀሳብ እየተከናወነ ባለው የመጽሃፍት ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር የተለያዩ ተቋማት መጽሃፍት እየለገሱ ይገኛሉ፡፡

በዛሬው እለትም አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከሰራተኞቹ፣አመራሮቹና አድማጭ ተመልካቾቹ ያሰባሰባቸውን ከ5ሺህ በላይ መጽሀፍትን  ማበርከቱን  የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ  በቀለ ሙለታ ተናግረዋል።

“መጽሐፍት ለአንባቢው ዓለሙና ወዳጆቹ ናቸው” ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ መጽሃፍት ያለፈውን፣ ያሁኑን ና የሚመጣውን ትውልድ በእውቀት ቅብብል እንደሚያስተሳስር አብራርተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የትውልድ የዕውቀት ማዕድ የሆኑትን መጽሐፍት ለቤተ መጽሃፍቱ እንዲያበረክት ዕድሉን በማግኘቱ በሠራተኞቹ ስም አመስግነዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ማቲዎስ እንሰርሙ በበኩላቸው፤ አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ  ላበረከታቸው መጽሃፍት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ለቤተ መጽሃፍቱ የሚደረገው መጽሃፍት የማሰባሰብ መርሃ-ግብር አበረታች ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

ከዚህ አኳያ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ40 ሺህ በላይ የሆኑ የዲጂታል ቤተ-መጽሐፍት ውጤቶቹን ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት አንባቢያን እንዲደርስ ማድረጉን ጠቁመዋል።

የመንግሥትና የግል ዩኒቨርሲቲዎች ለቤተ መጽሃፍቱ መጽሃፍትን በማበርከት ረገድ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ከ500 ሺህ በላይ መጻህፍትን ማበርከታቸው ተገልጿል፡፡

ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት የሚሆኑ መጻህፍትን የማሰባሰቡ ዘመቻ እስከ ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚቀጥልም ይታወቃል።

Amharic English