ግንቦት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ከአራት ሺህ በላይ የተለያየ ይዘት ያላቸው መጽሐፍት አበረከተ።
ለቤተ-መጽሐፍቱ እስካሁን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ መጽሐፍት መሰብሰባቸው ተገልጿል።
“ሚሊዮን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ” በሚል መሪ ሃሳብ ቤተ-መጽሐፍቱን ለማደራጀት መጽሐፍ የማሰባሰብ መርሃ ግብር ተቋማትና ግለሰቦች ምላሽ በመስጠት ላይ ናቸው።
የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ዛሬ ያበረከታቸው መጽሐፍት ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማህበራዊ፣ ጥንታዊ ታሪካዊ እና ሌሎች ይዘቶችን የሚያትቱ ናቸው ተብሏል።
የጽህፈት ቤቱ የአገልግሎትና መልካም አስተዳደር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለምጸሐይ ጳውሎስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትውልድን በእውቀት መገንባት አላማ ያለውን የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ኢትዮጵያ እውቀት መር ትውልድን ለማፍራት ጉልህ ሚና የሚኖረውን ቤተ-መጽሐፍት አስመርቃ ለአገልግሎት አብቅታለች ብለዋል።
የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ኃላፊው ኢንጂነር ውብአየሁ ማሞ በበኩላቸው መጽሐፍት በሕያው ቤታቸው ተሰባስበው ሲገኙ ትውልድን በእውቀት ለማነጽ ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸው ገልጸዋል።
እስካሁን ከ500 ሺህ በላይ መጽሐፍት መበርከቱንም አመልክተዋል።
ለቤተ-መጽሐፍቱ የሚሆኑ መጽሐፍት የማሰባሰቡ ዘመቻ እስከ ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም ይቆያል።
ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በወጪ የተገነባው የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ከታህሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል።
ቤተ-መጽሐፍቱ ሶፍት ኮፒን ጨምሮ ከአራት ሚሊዮን በላይ መጽሓፍትን የመያዝ አቅም አለው።