Skip to content Skip to sidebar Skip to footer

በኢትዮጵያ የኦስትሪያ ኤምባሲ ለአብርሆት ቤተ መፃሕፍት የተለያዩ መፃሕፍትን አበረከተ

ጥቅምት 3/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የኦስትሪያ ኤምባሲ የተለያዩ ይዘት ያላቸውን መፃሕፍት ለአብርሆት ቤተ መፃሕፍትን አበረከተ።

በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ዶክተር ሲሞን ናፕን ጨምሮ ሌሎች የኤምባሲው ተወካዮች በተገኙበት መፃሕፍቶቹ ለአብርሆት ቤተ መፃሕፍት ተበርክተዋል።

የተበረከቱት መጽሃፍት በኦስትሪያ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተሰባሰቡ ከ450 በላይ መፅሃፍት መሆናቸው ተገልጿል።

መፅሃፍቱን በማሰባሰብ ትልቁን ሚና የተወጡት በኦስትሪያ ኤምሲአይ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩት ፕሮፌሰር በላቸው ገብረወልድ ናቸው።

በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ዶክተር ሲሞን ናፕን ባስተላለፉት መልዕክት የንባብ ማዕከላትና ትምህርት ዓለም ለደረሰበት የምርምር ደረጃ ዋናው መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

ከልጅነታቸው ጀምሮ በቤተ መጽሐፍት የማንበብና የመጎብኘት ልምድ እንዳቸው የሚናገሩት አምባሳደሯ፤ ለትውልድ ግንባታና ለአገር ዕድገት የማንበቢያ ማዕከላት ትልቅ ድርሻ አላቸው ብለዋል።

በሁለገቡ የአብርሆት ቤተ መፃሕፍት ባደረጉት ጉብኝት ልዩ ልዩ ይዘት ያላቸውን ከ450 በላይ መፅሃፍትን በማስረከባቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ለሁሉም ጉዳዮች ቁልፍ መሳሪያ ለሆነው ትምህርት ትኩረት በመስጠት አንባቢ ትውልድ መገንባት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም አብርሆት ቤተመፃሕፍት የልጆች ማንበቢያ ክፍል መኖሩ ታዳጊዎች መጽሐፍትን እንዲያገላብጡ፣ የዕይታ አድማሳቸው እንዲሰፋና ዓለምን እንዲገነዘቡ ያስችላቸዋል ነው ያሉት።

ቤተ መፅሐፍቱ አሁንም በርካታ ግብዓቶች እንዲሚሻ ገልፀው፤ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን እንደ ፕሮፌሰር በላቸው መፃሕፍትን አሰባስበው እንዲለግሱ ጠይቀዋል።

አገር የሚገነባውና ልማት የሚረጋገጠው በትምህርት በመሆኑ ቤተ መፅሓፍትን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ፕሮፌሰር በላቸው ተናግረዋል።

ዕድገታቸው ትምህርት ቤትና ቤተ መፅሐፍት ባልተሟላበት ገጠራማ አካባቢ እንደነበር አውስተው፤ በዕውቀት የበለጸጉ አገር ተረካቢ ወጣቶችን ለማፍራት ትምህርትን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።

መፃሕፍቱ በኦስትሪያ ኤምባሲ በኩል ከሚያውቋቸው ዩኒቨርሲቲ ቤተ መፃሕፍት አሰባስበው ከኤምባሲው ጋር በመተባበር ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ምሁራን የትምህርት ዘርፉን በተለይ በገጠራማ አካባቢ ያልተማሩት እንዲማሩ፣ የሚማሩት እንዲበረቱ የመደገፍ ግዴታ አለባቸው ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በአዲስ አበባ ተቀማጭነታችውን ያደረጉ ኤምባሳዎች፣ ለዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት ኅላፊዎች አብርሆት ቤተ መፃሕፍትን ጨምሮ የተለያዩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መጎብኘታቸው ይታወሳል።

በዚህም የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ለቤተ መፃሕፍቱ መፃሕፈትን መለገስ ጀምረዋል።

Amharic English