Skip to content Skip to sidebar Skip to footer

የአብርሆት ቤተ መጽሐፍት የእውቀትን ታላቅነት ማሳያ፣ ማሰባሰቢያና ለሌሎች ማሰራጫ መንገድ ነው

ሚያዚያ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአብርሆት ቤተ መጽሐፍት የእውቀትን ታላቅነት ማሳያ፣ ማሰባሰቢያና ለሌሎች ማሰራጫ መንገድ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት “በአምስት ቀናት አምስት ሺህ መጽሐፍት” በሚል መርሃ ግብር ያሰባሰበውን ከአምስት ሺህ በላይ መጽሐፍት ለአብርሆት ቤተ መጽሐፍት አስረክቧል፡፡

መጽሐፍቱን የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና አስረክበዋል።

ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ጌትነት ታደሰ በወቅቱ እንዳሉት፤ ድርጅቱ በከናወነው የመጽሐፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ከእቅዱ በላይ አሳክቷል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የታየው ተነሳሽነትና የተገኘው ውጤት ለሌሎች ተቋማት አርአያ እንደሚሆን ገልጸው፤ ከነገ ጀምሮም “እድሜ ልክ” የተሰኘ የመጽሐፍ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር ይጀመራል ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የስራ አመራር ቦርድ አባል ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “ለአንድ ሀገር ስልጣኔ ትልቁ መሰረት እውቀት ነው፤ የእውቀት መሰረት ደግሞ መጽሐፍት ናቸው”  ሲሉ ተናግረዋል፡፡

መጽሐፍ እውቀትን ማሸጋገሪያ ትክክለኛና እውነተኛ መንገድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአብርሆት ቤተ መጽሐፍት ከተሰራባቸው ሶስት መሰረታዊ ዓላማዎች ውስጥ አንደኛው እውቀት ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ማሳየት እንደሆነም አስገንዝበዋል።

መጽሐፍትን በማሰባሰብ እውቀትን ማምጣትና ወደ ሌሎች ተቋማትና ግለሰቦች ማሰራጫ መንገድ አድርጎ መጠቀም ሌላኛው ግቡ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የአብርሆት ቤተ መጽሀፍትን በእውቀት ለመሙላት ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም ለአንድ ወር የሚቆይ የመጽሐፍ ማሰባሰቢያ መርሀ-ግብር እንደሚዘጋጅና እስከ አንድ ሚሊዮን መጽሀፍት ለማሰባሰብ እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።

በየቤቱ የተቀመጡ መጽሐፍትን በብዛት ሰብስቦ በማምጣት በሂደት በጥራት እንዲለዩ እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው የአብርሆት ቤተ መጽሐፍት እስከ አራት ሚሊዮን መጽሐፍ የመያዝ አቅም አለው ብለዋል።

ቤተ መጽሐፍቱ ገና ከጅምሩ በቀን  እስከ አምስት ሺህ ሰዎችን እያስተናገደ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ካለው ፍላጎት አንጻር በሌሎች አካባቢዎችም ተጨማሪ ቤተ መጽሐፍት እንደሚያስፈልግ አመላካች ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአብርሆት ቤተ መጽሐፍትን በጊዜያዊነት ተረክቦ እንዲያስተዳደረው መደረጉ ይታወቃል፡፡

Amharic English