Skip to content Skip to sidebar Skip to footer

ሚያዝያ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ)ለአብርሆት ቤተ መጽሐፍት የሚደረገው ድጋፍ ለቤተመጽሐፍቱ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የሚደረግ ድጋፍ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ አመለከቱ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ለአብርሆት ቤተመጽሐፍት የሚውል የመጽሐፍት ድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሐግብር ዛሬ አስጀምሯል።

መርሐግብሩን ያስጀመሩት የኢዜአ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ ይህ የመጽሐፍ ማሰባሰብ ድጋፍ በአገራችንና በአፍሪካም ትልቅ ለሆነው የአብርሆት ቤተ መጽሐፍት የሚደረግ ድጋፍ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

በንባብ ባህል ትውልድን የመገንባት ጉድለት ሀገርን በብዙ መልኩ ጎድቷል ያሉት አቶ ሰይፈ “ለአብርሆት ቤተ መጽሐፍት የሚደረገው ድጋፍ ለቤተመጽሕፍቱ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የሚደረግ ድጋፍ ነው” በማለት አስገንዝበዋል።

ወጣቱና መጪው ትውልድ ሀገሩን እንዲገነባ ለማስቻል መጽሐፍት የማሰባሰብ ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን በማመልከትም ዘመቻው በከተማ ደረጃ ብቻ ሳይሆን ኢዜአ ባሉት 36 ቅርንጫፎች በሁሉም ክልሎች የሚካሄድ ትልቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ዛሬ የተጀመረውም የድጋፍ ዘመቻ ከመስጠት ባለፈ እኛም ጭምር እንድናነብ እድል የሚሰጥ በመሆኑ ከተቋሙ አጋር አካላት ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በኢዜአ አማካኝነት ለአብርሆት ቤተመጽሐፍት የሚደረገው የመጽሐፍት ድጋፍ ሳምንቱን ሙሉ የሚቀጥል ሲሆን ከተቋሙ ሰራተኞች በተጨማሪ አጋር አካላትም እንደሚሳተፉበት ተመልክቷል።

Amharic English