Skip to content Skip to sidebar Skip to footer

ለአብርሆት ቤተመጽሐፍት ኢትዮጵያዊያን ሁሉ መጽሐፍ እንዲለግሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ

መጋቢት 30/2014/ኢዜአ/ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ድጋፍ እንዲያደርጉና ትውልድን ለማነጽ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ።

የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ከግለሰቦችና ከተለያዩ ተቋማት መጻሕፍት ተበረክቶለታል።

ለቤተ-መጻሕፍቱ በተደረገው ድጋፍ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተገኝተዋል።

በእንግሊዝ አገር የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርቷን የምትከታተለው ወጣት ቤተልሔም ሰሎሞን በ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ 5 ሺህ 200 መጻሕፍት አስረክባለች።

በቀጣይም ለቤተ-መጻሕፍቱ ከሰዎች በማሰባሰብ የምታደርገውን አብርክቶ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግራለች።

በተመሳሳይም በጡረታ ላይ የሚገኙት አምባሳደር ማርቆስ የተባሉ ግለሰብ ለአርባ ዓመታት ያጠራቀሙትን ኢንሳይክሎፒዲያን ጨምሮ 904 መጻሕፍት ለግሰዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበሩና ሕይወታቸው ያለፈ ግለሰብ፤ በስማቸው ቤተሰቦቻቸው 997 መጻህፍትን ለቤተ-መጻሕፍቱ ሰጥተዋል።

ማይክሮሊንክ የተሰኘ ተቋም 287 መጻሕፍት ያበረከተ ሲሆን የአብሮሆት ቤተ-መጻሕፍት ከግለሰቦችና ከተለያዩ ተቋማት በድምሩ 7 ሺህ 388 መጻፍት ዛሬ ተበርክቶለታል።

በመጻሕፍት ርክክቡ ሥነ-ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፤ መጻሕፍትን ላበረከቱ ግለሰቦችም ምስጋና አቅርበዋል።

ያበረከቱትም አስተዋጽዖ ለሌሎች ሰዎች አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

 “በመስጠትና በማካፈል ትውልድን ማነጽ ይቻላል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤተ-መጻሕፍትን መገንባት ብቻ ጥቅም እንደሌለው ገልጸው ቤተ-መጻሕፍቱን ሙሉ ለማድረግ መጻሕፍት አሰፈላጊ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በቀጣይ ወር በርከት ያሉ መጻሕፍትን ለማሰባሰብ መታቀዱን ተናግረው ኢትዮጵያውያን አሁንም የመጻሕፍት አበርክቷቸውን እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ቤተ መፅሐፍቱ ዛሬ የተደረገለት የመጻሕፍት ድጋፍን ጨምሮ እስካሁን 12 ሺህ መጻሕፍት ድጋፍ ተደርጎለታል።

መጻሕፍቱን ማሰባሰብ የተቻለው በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቋቋመ ኮሚቴ አማካኝነት መሆኑ ታውቋል።

አብርሆት ቤተ-መጻሕፍት 4 ሚሊየን መጻሕፍት እንደሚያስፈልጉት ተመላክቷል።

በአዲስ አበባ ከተማ አራት ኪሎ አካባቢ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው አብርሆት ሁለገብ ቤተ መጽሐፍት ታህሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ተመርቆ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል።

በ19 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ቤተመጽሐፍቱ በ4 ወለሎቹ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን መጸሐፍትን መያዝ የሚችል 1 ነጥብ 5 ኪ.ሜ የሚረዝም መደርደሪያ አለው።

Amharic English