Skip to content Skip to sidebar Skip to footer

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 9/2015 የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት 4 ሺህ ልዩ ልዩ መጽሐፍቶችን አበረከተ።

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ሙሉጌታ ተፈራ፤ መጽሃፍቶቹን ለአብርሆት ቤተ-መጻህፍት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ውብአየሁ ማሞ አስረክበዋል፡፡

የአብርሆት ቤተ-መጽሃፍት መጪው ትውልድ በዕውቀት የሚጎለብትበት ዘመን ተሻጋሪ ቅርስ በመሆኑ የሁላችንም ተሳትፎና ድጋፍ ያስፈልገዋል ሲሉ አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል።

በመሆኑም የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ከተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ሰራቶች ያሰባሰበውን ለቤተ መጽሃፍቱ 4 ሺህ ልዩ ልዩ መጽሃፍቶችን አበርክቷል ብለዋል።

በዋናነት የመማሪያ፣ ለአዋቂዎችና ለታዳጊዎች ጠቅላላ እውቀትን የሚያስገኙ፣ ለጥናት እና ምርምር አጋዥ የሆኑ መጻህፍቶችን አበርክተናልም ነው ያሉት።

የአብርሆት ቤተ-መጻህፍት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ውብአየሁ ማሞ፤ በቢሮው ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

በቤተ-መጻህፍቱ ለሚጠቀሙ አንባቢያን ልዩ ልዩ እውቀቶችን የሚያስጨብጡ ጠቃሚ መፅሃፍት መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

እስካሁን በርካታ ተቋማትና ግለሰቦች በርካታ መጽሐፍቶችን ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው በቀጣይም እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።

ቤተ-መጽሐፍቱን ለማሟላት 4 ቢሊዮን መጽሐፍቶች የሚያስፈልጉ በመሆናቸው ተቋማትና ግለሰቦች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአንድ ጊዜ ከ2 ሺህ በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችለው የአብርሆት ቤተ መፃህፍት ከማንበቢያ ስፍራ በተጨማሪ የስብሰባ አዳራሽ፣ ካፍቴሪያ፣ የህፃናት ማንበቢያና ሌሎችንም ያካተተ ዘመናዊ መካነ ንባብ ነው።

Amharic English