ሁለት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት የተለያዩ መጻሕፍት አበረከቱ
ግንቦት 6/2014 (ኢዜአ) “ቪ ኤስ ኦ ” እና “እነሆ ፍቅር ” የተባሉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት የተለያዩ መጻሕፍት አበረከቱ።
ሁለቱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ያበረከቷቸውን የተለያዩ መጻሕፍት የአዲስ አበባ ከተማ ኅብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሙሰማ ጀማል ተረክበዋል።
የቪ ኤስ ኦ ዓለም አቀፋዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት የሎጂስቲክ ኦፊሰር ማሞ አሸናፊ፤ ትውልድ በቅብብሎሽ ለሚገነባበት ቤተ-መጽሐፍት መጽሐፍቶችን በማበርከታችን ደስተኞች ነን ብለዋል።
በዛሬው እለት ከ1 ሺህ በላይ መጽሐፍት መለገሳቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ከመንግስት ጋር በመተባበር ድርጅታቸው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ የራሱን እገዛና አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የእነሆ ፍቅር በጎ አድራጎት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ማህሌት ወርቁ፤ አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር ቤተ-መጽሐፍት መገንባትና መጽሐፍትንም ማሟላት ይገባል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ የአሁኑ ትውልድ አደራና ኃላፊነት ስላለበት ድርጅታቸው ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት 1 ሺህ መጽሐፍት ለግሷል ሲሉ ተናግረዋል።
በቀጣይም ከተለያዩ አካላት መጽሐፎችን የማሰባሰብ ሥራ በማከናወን አበርክቷችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የኅብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ምክትል ኮሚሽነር ሙሰማ ጀማል ሁለቱም ድርጅቶች ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
ለሀገር ሁለንተናዊ የግንባታ ሂደት እውቀትን የተላበሰ ትውልድ መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ የመጻሕፍት አበርክቶ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
የአብርሆት ሁለገብ ቤተ-መጽሐፍት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ ሲሆን ታህሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ሥራ መጀመሩ ይታወሳል።
ለግዙፉ እና ዘመናዊው ቤተ-መጽሐፍት ከግለሰቦችና የተለያዩ ተቋማት እንዲሁም ማኅበረሰቡ የመጽሐፍት ልገሳ በመደረግ ላይ ይገኛል።