ግንቦት 17/2014/ኢዜአ/ የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት 13 ሺህ 445 መጽሃፍትን አበረከተ፡፡
ድርጅቱ ከሰራተኞቹና ከተለያዩ ከድርጅቶች ያሰባሰበውን መጽሃፍ ነው ዛሬ ያበረከተው፡፡
መጽሃፍቱንም የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሩክ ሃብቴ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትን ወክለው ለመጡት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አስረክበዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በዚሁ ወቅት ለቤተ መጽሃፍቱ የተበረከቱ መጽሃፍቶች ሁሉንም ዘውግ ያካተቱና ለምርምር ጭምር የሚረዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ድርጅቱ 13 ሺህ 445 መጽሃፍትን ያበረከተ መሆኑን ጠቅሰው፤ መጽሃፍት የማሰባሰቡን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
መጽሃፍትን በመለገስ የነገ አገር ተረካቢ ትውልድን መቅረጽ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ድርጅቱ ያደረገው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም በቤት ውስጥ የተቀመጡ መጽሃፍትን ወደ ቤተመጽሃፍት ወስዶ በመለገስ ለሁሉም ዜጋ እንዲበቁ ማድረግ እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው፤ አብርሆት ቤተ መጽሃፍት በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተጻፉ መጽሃፍትን በማሰባሰብ ረገድ ትልቅ እድል ይዞ መጥቷል ብለዋል።
ከዚህ አኳያ የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ዛሬ ያበረከታቸው መጽሃፍት የኢትዮጵያን ቋንቋና የባህል ብዝሃነትን የሚያመላክቱ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
ትውልዱ አንባቢ አይደለም ብሎ ከመተቸት ይልቅ ለንባብ የሚሆን ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
ትውልዱ የተፈጠሩለትን ምቹ ሁኔታዎች በአግባቡ መጠቀም እንደሚችል የአብርሆት ቤተ መጽሃፍት በግልጽ ማሳየቱንም አብራርተዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ሌሎች ተቋማት ለአብርሆት ቤተ-መጽሃፍት የሚሆኑ መጽሃፍትን በማበርከት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ተቋማት በተሰማሩበት የስራ መስክ ያሉ መጽሃፍትን በመለገስ ለጥናትና ምርምር መጎልበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዳለባቸውም ነው ያሳሰቡት፡፡
ለአብርሆት ቤተ-መጽሃፍት የሚሆኑ መጽሃፍትን የማሰባሰቡ ዘመቻ እስከ ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ ም እንደሚቀጥል ተገልጿል።