ሰኔ 09/2014(ኢዜአ) የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት በትውልድ ላይ መሥራት እንዳለብን ያሳሰበና ከሰራን መለወጥ እንደምንችል ያመላከተ ነው ሲሉ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ተናገሩ።
ከንቲባው ቤተ-መጽሐፍቱን ለማገዝና ተሞክሮ ለማስፋት የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል።
ከንቲባው ቤተ-መጽሐፍቱን በመጎብኘት በከተማ አስተዳደር ከንቲባ ደረጃ የመጀመሪያ እንደሆኑም ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በፓርላማ ንግግራቸው በአገሪቱ በርካታ ፕሮጀክቶች መከናወናቸውንና በተለይ በአዲስ አበባ ትውልድ የሚለውጥ ሥራ መሰራቱን ጠቁመዋል።
እነዚህን ፕሮጀክቶች የለውጡ አመራር በመጎብኘት መነሳሳትን እንዲፈጥሩ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ በጉብኘታቸው ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ቤተ-መጽሐፍቱ ለውጡ ካስገኛቸው ፍሬዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ባለፉት ጊዜያት በሰዎች አዕምሮ የመሥራትና ያለንን ሃብት ተጠቅመን አገር የምንለውጥበትን ጊዜ አባክነናል ሲሉም ተናግረዋል።
አሁን የመለወጥና በሰዎች አዕምሮ ላይ መሥራት ያለበት ጊዜ በመሆኑ የተሰጠውን እድል በማስፋትና በአግባቡ መጠቀም የለውጥ አመራሩ ድርሻ መሆኑን አስረድተዋል።
“ቤተ-መጽሐፍቱን ለማገዝና ተሞክሮውን ለማስፋት የበኩላችንን እንወጣለን” ሲሉም አረጋግጠዋል።
በለውጡ የተገኘውን ፍሬ በማገዝ በሁሉም ክልል ማስፋትና ማዳረስ ያለብን አሁን ያለነው አመራሮች በመሆናችን የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
“ጠንክረን ከሰራንና ኃላፊነታችንን በአግባቡ ከተወጣን ኢትዮጵያን ከዚህ በላይ ማሳደግ እንችላለን’ ሲሉም ከንቲባው ተናግረዋል።
የቤተ-መጽሐፍቱ ዲጂታል ላይብረሪያን ዋቁማ ኡማ፤ የአብርሆትቤተ-መጽሐፍት ተሞክሮ በሁሉም ክልሎች መስፋት አለበት ብለዋል።
የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ በከተማ ደረጃ የአብርሆትን ቤተ-መጽሐፍት በመጎብኘት ቀዳሚ መሆናቸውን በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ለዚህም ከፍተኛ አመራሩ ተሞክሮውን በመቃኘትና ሁሉም በተሰማራበት ለትውልድ የሚተርፍ ሥራ በመሥራት ኢትዮጵያን ሊያግዝ ይገባል ብለዋል።
ሁሉም የአገሪቱ አመራር ቤተ-መጽሐፍቱን በመጎብኘትና በማገዝ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።