ግንቦት 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ይዘት ያላቸውን ከአንድ ሺህ በላይ መጽሐፍት ለአብርሆት ቤተ- መጽሐፍት አበረከተ፡፡
መጽሐፍቱን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ደረጀ እንግዳ ለአዲስ አበባ ባህል፣ ቱሪዝምና ኪነ-ጥበብ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው አስረክበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት በዚሁ ጊዜ የንባብ ባህል መጎልበት በተለይ ለትምህርት ጥራት መሻሻል ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ይህን ታሳቢ በማድረግ ለቤተ-መጽሐፍቱ ማስረከቡን ገልጸው፤ መጽሐፍቱም በዋናነት የሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ የጠቅላላ ዕውቀትና የስነ-ልቦና ይዘት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍትን በዲጂታል መረጃ ለማደራጀት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ የባህል፣ ቱሪዝምና ኪነ-ጥበባት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎች የሚያበረክቱት መጽሐፍት አንባቢ ትውልድን ለመፍጠር የሚኖረው ሚና የላቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡