Skip to content Skip to sidebar Skip to footer

ግንቦት 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ለአብርሆት ቤተ መጽሃፍት ከሰራተኞቹና ከተለያዩ ታዋቂ ግለሰቦች ያሰባሰበውን ከ5ሺህ በላይ መጽሃፍትን ነገ ያስረክባል።

የአብርሆት ቤተ መጽሃፍት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

ቤተ መጽሃፍቱን በተለያዩ መጽሃፍት ለማደራጀትም ከሚያዚያ 28 እስከ ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም የሚቆይ የማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተቀርጾ እየተሰራ ይገኛል።

መርሃ ግብሩን ለማሳካት የተለያዩ ተቋማት ተሳትፏቸውን በማጠናከር መጽሃፍትን አሰባስበው በማስረከብ ላይ ናቸው።

በዚህም ኢዜአ ግዙፉን የአብርሆት ቤተ መጽሃፍት ለማደራጀት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ከአርቲስት ደበበ እሸቱና ከገጣሚና ጸሃፈ-ተውኔት አያልነህ ሙላቱ በተጨማሪ ከሰራተኞቹና ከተለያዩ ግለሰቦች ያሰባሰበውን ከ5 ሺህ በላይ መጽሐፍት ነገ ያስረክባል።

አርቲስት ደበበ እሸቱ እና ገጣሚና ጸኃፈ ተውኔት አያልነህ ሙላት በኢዜአ በኩል ለአብርሆት ቤተመጽሃፍ እንዲውሉ በማሰብ የፃፏቸውን ስራዎች ጨምሮ የተለያዩ መጽሐፍትን መለገሳቸው ይታወሳል።

ለአብርሆት ቤተ-መጽሃፍት እንዲውል ለኢዜአ ያስረከቡት የእጅ ድርሰቶችም ለበርካታ ኢትዮጵዊያን እንዲደርስ በማሰብ እንደሆነ መጽሃፍቶችን ባስረከቡበት ወቅት መናገራቸው ይታወሳል።

ትውልዱም ይህን በጎ ስራ አጠናክሮ መቀጠልና መጽሐፍትን በመለገስ አሻራውን እንዲያኖር መምከራችውም እንዲሁ።

Amharic English